ልጅ ለመውለድ እየሞከሩ ነው? ስለ ወሲብ የሚጠየቁ 8 የተለመዱ ጥያቄዎችና ሳይንሳዊ ምላሾቻቸው
ልጅ ለመውለድ እየሞከሩ ነው? ስለ ወሲብ የሚጠየቁ 8 የተለመዱ ጥያቄዎችና ሳይንሳዊ ምላሾቻቸው
ልጅ ለመውለድ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ከተለያዩ ሰዎች ብዙ ዓይነት ምክሮችንና ወሬዎችን ሰምተው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሳይንሱና ሕክምናው በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ምን ይላል? በብዛት ለሚነሱ 8 ጥያቄዎች በማስረጃ የተደገፉ ሳይንሳዊ ምላሾችን እንደሚከተለው አቅርበናል።
1️⃣ በየቀኑ ግንኙነት ማድረግ አለብን?
ምላሽ፦ አዎ፥ ግንኙነት ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን ከሁሉ በላይ አስፈላጊው ነገር የግብረ ስጋ ግንኙነት መደረግ ያለበት የመራቢያ ጊዜ ወይም (Fertile Window) በሚባለው ወቅት ላይ ነው። ይህም የሴቷ እንቁላል ከመውጣቱ ወይም ከመለቀቁ በፊት ያሉትን 5 ቀናት እና እንቁላል የሚለቀቅበትን ቀን ያካትታል። በዚህ ወቅት የግብረ ስጋ ግንኙነት ማድረግ የማርገዝ እድልን በእጅጉ ይጨምራል።
2️⃣ ከግንኙነት በኋላ ሽንት ለመሽናት መቆየት አለብኝ?
ምላሽ፦ መቆየት አያስፈልግም። ከግንኙነት በኋላ ወዲያውኑ መሽናት እርግዝና የመፈጠር ዕድል ላይ ምንም የሚያመጣው ተጽዕኖ የለም። እንዲያውም የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽንን (UTI) ለመከላከል ይረዳል። የዘር ፈሳሹ (Sperm) ሽንት ከመሽናትዎ በፊት በፍጥነት ወደ ማህፀን ውስጥ ይገባል።
3️⃣ ከግንኙነት በኋላ በጀርባዬ መተኛት ይኖርብኛል?
ምላሽ፦ አስፈላጊ አይደለም። የዘር ፈሳሽ ወይም ስፐርም በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ወደ ማህፀን በር መድረስ ይችላል። በጀርባ መተኛት የማርገዝ እድልን እንደሚጨምር የሚያሳይ ምንም አይነት ጠንካራ ሳይንሳዊ ማስረጃ የለም።
4️⃣ ከወሲብ በኋላ ባሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ወሲብ ማድረግ ፅንሱ ማህፀን ላይ እንዳይጣበቅ ያደርጋል?
ምላሽ፦ በአሁኑ ወቅት ያለው ሳይንሳዊ መረጃ እንደሚያሳየው ግንኙነት ማድረግ ፅንስ በማህፀን ግድግዳ ላይ እንዳይጣበቅ ወይም ኢምፕላንቴሽንን (Implantation) አያግደውም። ሐኪምዎ በተለየ ሁኔታ ካልከለከለዎት በስተቀር ግንኙነት ማድረግ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው።
5️⃣ ለእርግዝና ተመራጭ የሆነ የወሲብ አቅጣጫ (Position) አለ?
ምላሽ፦ እርግዝናን ይጨምራል ተብሎ በሳይንስና ምርምር የተረጋገጠ የተለየ የወሲብ አቅጣጫ ወይም Position የለም። ዋናው ነገር የወንድ የዘር ፈሳሽ ወደ ማህፀን በር መድረሱ ነው።
6️⃣ ለማርገዝ በምንሞክርበት ወቅት ማለስለሻዎችን (Lubricants) መጠቀም እንችላለን?
ምላሽ፦ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። አብዛኞቹ የተለመዱ ማለስለሻዎች ወይም ሉብሪካንቶች የስፐርም እንቅስቃሴን ሊቀንሱ ይችላሉ። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለዘር ፍሬ ህዋስ ደህንነታቸው የተረጋገጠ “Fertility-friendly” ወይም የዘር ፍሬ ፈሳሽን የማይጎዱ (Sperm-safe) ማለስለሻዎችን ይምረጡ።
7️⃣ ሴቶች የስሜት ጫፍ (Orgasm) ላይ መድረስ የማርገዝ እድልን ይጨምራል?
ምላሽ፦ ሴቶች በግንኙነት ወቅት የእርካታ ጫፍ ላይ መድረሳቸው ለጤናማ የወሲብ ሕይወት ጠቃሚ ቢሆንም፤ እርግዝና የመፈጠር ዕድልን እንደሚጨምር የሚያሳይ ጠንካራ ሳይንሳዊ መረጃ የለም።
8️⃣ ግለ-ወሲብ (Masturbation) የማርገዝ እድልን ይቀንሳል?
ምላሽ፦ አይቀንስም። ግለ-ወሲብ ጤናማ በሆኑ ሰዎች ላይ መሃንነትን አያስከትልም፣ ወይም የመውለድ አቅምን እንዲሁም የማርገዝ ዕድልን አይቀንስም። ነገር ግን የራሱ የሆኑ ሌሎች ጉዳቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ መዘንጋት የለብንም።
📌 ዋና ነጥብ፦
ትኩረትዎ እንቁላል የሚለቀቅበትን ትክክለኛ ጊዜ በማወቅ፤ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን በመከተል ላይ፣ እንዲሁም ውጥረትና ጭንቀትን በመቀነስ ላይ ይሁን።
እድሜዎ ከ35 በታች ሆኖ ለ12 ወራት (ወይም ከ35 በላይ ሆኖ ለ6 ወራት) ሞክረው እርግዝና ካልተሳካ፤ የጤና ባለሙያ ማማከር ይኖርብዎታል።
🔍 ምንጮች እና የምርምር ማጣቀሻዎች (Verified Scientific Sources):
- Clearblue – Top 8 sex questions about trying to conceive
- American College of Obstetricians and Gynecologists (ACOG) – Trying to Get Pregnant
- CDC – Reproductive Health & Infertility
- Office on Women’s Health (U.S. HHS) – Getting Pregnant
- American Society for Reproductive Medicine (ASRM) – Optimizing Natural Fertility